በጎንደር ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከጎሰልፍ የተሰጠ መግለጫ
(የጎንደር-ጭልጋ- ሰራቫው ስምምነት መነሻና መዳረሻ)
(ቁጥር 4)

ሰላም፣ልማትና ፍትህ ለጎንደር ማህበር (ጎሰልፍ) መቀመጫውን በሰ/አሜሪካ አድርጎ በጎንደር ህዝቦች ሰላም፣ልማትና ፍትህ መስፈን ዙሪያ ተቀዳሚ አላማውን አንግቦ ሊሰራ የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በተለይም ደግሞ ባለፉት በርካታ አመታት ከቅማንት ህዝብ ራስ አስተዳደር ጥያቄ አፈታት ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ባለ ሰው ሰራሽ ግጭት ሳቢያ ሁለመናቸው እየተናጋ የሚገኙትን ምእራብና ማእከላዊ ጎንደር ዞኖች ማእከል ያደረጉ ቀጠናዊ ደብዳቤዎችንና መግለጫዎችን በተከታታይ ለህዝብና መንግስት ይፋ ሲያደርግ መቆየቱ አይዘነጋም። ዛሬም እንደትናንቱ አምባገነናዊና ጸረ-ህዝብ አካሄድ በጠፈነገው የመፍትሄ ስልትና እንዲሁም የህዝቦችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ስምምነት፣ ውሳኔና እርምጃ በመጥፋቱ ምክንያት አካባቢው ወደተለመደው ትርምስና ቀውስ እንዲገባ ሆን ተብሎ በተደራጀና በታቀደ መልኩ እየተሰራ ስለመሆኑ በእየጊዜው ከስፍራው የምናገኛቸው መረጃዎች፣ መንግስት ከሚሰጣቸው መግለጫዎችና በማህበራዊ መገናኛዎች እየተለቀቁ ከሚገኙት ዘገባዎች ድምር ውጤት ለማወቅ ችለናል። ስለሆነም ጎሰልፍ ከቆመለት አላማ አኳያ የጎንደር ህዝቦች ሰላም፣ልማትና ፍትህ እንዳይናጋ ካለው ጥልቅ ፍላጎት በመነጨ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይም ደግሞ በየትኛውም መመዘኛ ጉዳዩ በቀዳሚነት ለሚመለከታቸው የጎንደርና አካባቢው ህዝቦች እንዲሁም ግጭቱ እንዲያገረሽ ሃላፊነት በጎደለው መንገድ ተግተው እየሰሩ ለሚገኙት መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ አካላት በሙሉ በአካባቢው ያንዣበበውን ጊዜ የማይሰጥ አደጋ አስመልክቶ ያለውን እምነትና መልእክት በዚህ ጽሁፍ ለመግለጽና ለማሳሰብ ይገደዳል።
የቅማንት ህዝብ ራስ አስተዳደር ጥያቄ እንደማንኛውም ህዝብ በስራ ላይ ያለውን ህገ-መንግስትና ሌሎች ህጎች መሰረት አድርጎ ለሚመለከታቸው የክልልና ፌዴራል መንግስት አካላት ስለመቅረቡ ብሎም ከስንት ውጣ-ውረድ፣ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በኋላ አስተዳደሩ 69 ቀበሌዎችን አካቶ እንዲመሰረት በአዋጅ ቁጥር 255/2010 በክልሉ መንግስት በኩል የተደነገገ ስለመሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። በጥያቄው ባለቤትና በምላሽ ሰጪው አካል መካከል አልግባባ ብሎ የዘለቀው ጉዳይ ታዲያ ምንድነው ከተባለ ህዝቡ ወስኖ ያደረባቸው የሶስቱ የመተማ ቀበሌዎች (ጉባይ፣ሌንጫና መቃ) በዚህ አዋጅ አብረው አለመካተታቸውና ውሳኔውም አጠቃላይ የቅማንቱን ህዝብ እንደህዝብ ከሁለት የከፈለ የሆነበት ምክንያትና ከርትእ ያፈነገጠ መሆኑ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የአማራ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን የ69 ቀበሌ አዋጅ ባጸደቀበት ወቅት ስለአካባቢው እውቅና ያላቸው ተወካዮች ውሳኔው የህዝብን ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆንና በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ ከአድልኦ የጸዳ መሆን እንዳለበት አበክረው እያሳሰቡ ሰሚ በማጣት ም/ቤቱ ራሱን ከህዝብ ድምጽ በላይ አድርጎ በመቁጠር አዋጁን በማውጣቱም ጭምር ነው። ከዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ቢኖር የህዝብ ተወካዮች ም/ቤቶችና የሚያወጧቸው ህጎች የተፈጠሩበት ዋና አላማ የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ እንጅ የአንድን የፖለቲካ ቡድን ፍላጎትና ህልም ለማሳካት በፍጹም አይደለም። የህዝብ መገልገያ መንግስታዊ ተቋማትና ህጎች የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም ለመድፈቅ ስራ ላይ እንደመሳሪያ ከዋሉ ዋናውንና ሊፈጠሩለት የሚገባውን አላማ ስተዋል ማለት ነው። ሶስቱ የመተማ ቀበሌዎች ከነዋሪዎቹ ፍላጎት በተጻራሪ ተቆርጠው የሚቀሩበት ህጋዊም ሆነ ነባራዊ ምክንያት መሬት ላይ አይገኝም።
በተሳሳተና ቅንነት በጎደለው መንገድ የቅማንት ህዝብ ጥያቄ ሊፈታ ስለተሞከረ በቀጠናው አላስፈላጊ ግጭቶች በተደጋጋሚ በመከሰታቸው ምክንያት በርካቶች በግፍ መገደላቸው፣ መፈናቀላቸው፣ ሀብት አልባ መሆናቸው፣ መታሰራቸው፣ መደፈራቸው፣ ወዘተ አይረሳም። የቅማንት ህዝብ ጥያቄ አስተባባሪ ተወካዮችም ራሳቸውን ከጥፋት ለመታደግ ከመኖሪያ ቤታቸው ተሰደው ኑሯቸውን ጫካ ውስጥ በማድረግ ለበርካታ ወራት ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ የአማራ ክልል መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት ባወጁት የምህረት አዋጅ መሰረት ከ9 ወራት በፊት (ጥቅምት 2012 አ/ም) በጭልጋ ወረዳ ሰራቫ መከላከያ ካምፕ በተደረገ ስብሰባ የቅማንት ህዝብ ተወካዮች፣ በፌዴራል ደረጃ የሰላም ምንስትሯ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የመከላከያ ኢታማጆር ሹም ጄኔራል አደም ሙሃመድ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ታሪካዊ የሚባል የሰላም ድርድር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ይህ ድርድር የመንግስት ሚዲያ ሽፋን የተሰጠውና “የጋራ ጥምር ኮሚቴ” ተቋቁሞ እስከአሁን ድረስ የቀጠለ ነው። ሁላችንም በጥምር ኮሚቴውና በሰላም ድርድሩ ጅምርና ሂደት ላይ በእጅጉ ተስፋ የሰነቅንበት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የፌዴራል መንግስት ተወካይ የሰላም ምንስትሯ በዚህ ጥምር ኮሚቴ ውስጥ መኖራቸው ለዘመናት ያለአግባብ እየተጓተተ የሰው ህይወትና ንብረት እየቀጠፈ የሚገኘውን የሶስቱ የመተማ ቀበሌዎች አለመካተት ጉዳይ በህዝቦች ፍላጎት የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ፣ የጎንደር ህዝቦች ሰላም፣ልማትና ፍትህ እንዲረጋገጥ ትክክለኛ መስመር ይዘረጋሉ የሚል ከፍተኛ ፍላጎትና ተስፋ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩን የክልሉ መንግስት ተወካዮችና የቅማንት ህዝብ ተወካዮች በመከላከያ አጋዥነት በሂደት እንዲቋጩት ጥለውት መውጣታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የጥምር ኮሚቴው የተስማማባቸውን አምስት ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ እንደነገሩ እንደሞከረ ሲገለጽ በስድስተኛ ደረጃ 3ቱን የመተማ ቀበሌዎች በተመለከተ ግን በጋራ ወርደው ነዋሪውን ህዝብ እንደሚያወያዩና ህዝብ የወሰነውን ሊያከብሩ ስምምነት አድርገው እንደነበር አረጋግጠናል። ይሁን እንጅ ነገሮች በመጀመሪያው የሰላም ድርድር መንፈስ መሄድ እንደተሳናቸው፣ በቅማንት ህዝብ ተወካዮች ላይ አላስፈላጊ ጫና በመፍጠር በጋራ ወደህዝብ ለመውረድና ለማወያዬት የተስማሙትን በመሰረዝ የክልሉ አንዳንድ ባለስልጣናት ቀጭን ትእዛዝና ማስፈራሪያ እየሰጡ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለምን በጋራ ህዝብን ለማወያዬት እንደተፈራና ወደተለመደው የጥፋት አዙሪት ለመግባት ይህን ያህል መታሸት እንደተፈለገ ግን ግልጽ አይደለም። ከዛም አልፎ የክልሉ መንግስት ልዩ ሃይል ከፋኖና ከአንዳንድ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በመቀናጀት በመተማና ቋራ አካባቢ ህግ ለማስከበር ሽፍታ መያዝ አለብን በሚል ሽፋን በንጽኋን አርሶ አደሮች ላይ ጭፍጨፋ እንደፈጸሙና የቁም ከብቶችን በመዝረፍ እንዲሁም በሚዘገንን ሁኔታ በጥይት በመግደል አካባቢውን ወደማንፈልገው ቀውስ ለማስገባት ትልቅ ሸፍጥ እየተሰራ እንደሆነ ተነግሯል፤ተዘግቧልም። በርካታ ቅማንቶች በዚሁ አካባቢና በሌሎች ቀጠናዎች እየታደኑ እየታሰሩ እንደሆነም እየተነገረ ነው። የህግ የበላይነት መከበር ለጎንደር ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የህልውና ጉዳይ እንደሆነ የምናምን ቢሆንም ህግ በማስከበር ሽፋን የህዝብን ሰላም፣ልማትና ፍትህ ማናጋት ግን በፍጹም ተቀባይነት የለውም እንላለን። ህዝብ የደገፈውን ሌባ ነው ብሎ የልማታዊና የሰላማዊ አርሶ አደሮችን ህይወት ማቃወስ የመንግስት ተቀዳሚ አላማ ሳይሆን በራሱ “ሽፍትነት” ይሆናል።
በሌላ በኩል ለነጭ ፖለቲካ ፍጆታ እየዋለና የጎንደርን ህዝቦች ሰላም፣ልማትና ፍትህ እያዛባ የሚገኘው በቅማንት ምድር “የህወሃት” እጅ አለ የሚለው የተሳሳተና የተንኮል ፕሮፓጋንዳ ዛሬም ድረስ መቀጠሉ ነው። አንድም አይነት የተጨበጠ የሚታይ የሚዳሰስ ማስረጃ ያልቀረበበት ጉዳይ ቢሆንም ዛሬም ምስኪን የቅማንት አርሶ አደር እየተንገላታበት እንደሚገኝ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል። እንደኢሳትና 360 አይነት ሃላፊነት የጎደላቸው ሚዲያዎች፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን (ለምሳሌ ረ/ፕሮፌሰር አበባው) እና በሃይማኖት ሽፋን የሚነግዱ ግለሰቦች (ለምሳሌ ዘመድኩን በቀለ) የተዛባና መርዛማ ህዝብ አስጨራሽ ንግግራቸውን እንደቀጠሉበት ነው። ከዚህ በተጓዳኝም በካድሬ ሰነድ በተደገፈ ዘመቻ የቅማንትና አማራ ምስኪን ገበሬዎች “ህወሃትን” እንዲወጉ ለዘመቻ ዝግጅት እንዲያደርጉ ካለባቸው ችግር በላይ ተጨማሪ ጫናና ውጥረት እየፈጠሩባቸው እንደሆነ ተደጋግሞ እየተነገረ ነው። ይህ አካሄድ ስልጣን ኮርቻ ላይ ለሚቆዬው ሃይል ይጠቅም ካልሆነ በስተቀር ለወንድማማች ህዝቦች ሰላምና አንድነት የሚፈይደው ነገር ስለሌለ ማንኛውም ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፈታት ይኖርበታል ብለን እናምናለን።
በመጨረሻም ጎሰልፍ የሚከተሉት ጥንቃቄዎችና እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወሰዱ በጥብቅ ያሳስባል፤
1) ከሁሉም በላይ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ውስጥ የምትገኙ የህዝብ ሃላፊነት የያዛችሁ ባለስልጣናት በሙሉ ስልጣን የህዝብ ማገልገያና አላፊም ጭምር ስለሆነ ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥታችሁ የቅማንት ህዝብ ራስ አስተዳደር “ጥምር ኮሚቴው” በተስማማው አግባብ ተሂዶ በህዝቦች ፈቃድ እንዲቋጭ በማድረግ የጎንደር ሰላም፣ልማትና ፍትህ እንዲረጋገጥ እንድታደርጉልን መከራ በሚፈራረቅባቸው የጎንደር ህዝቦች ስም እንጠይቃለን።
2) የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ህዝቦችን በገለልተኝነትና በፍጹም ወታደራዊ ስነ-ምግባር የማገልገል ሃላፊነታቸውን እንዳይዘነጉና የአንድ የፖለቲካ ቡድን መሳሪያ በመሆን ጭቁኖችን ጨምረው እንዳይጨቁኑ ከሚገፉት ጎን እንዲሰለፉ አጥብቀን እናሳስባለን።
3) በአማራ ክልል ውስጥም ሆነ ከክልሉ ውጭ እንዲሁም ከአገር ውጭ ሁናችሁ ራሳችሁን በተለያዬ መልኩ አደራጅታችሁ ስለጎንደር ህዝቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይመለከተናል ብላችሁ የምትሰሩ ሃይሎች፣ቡድኖች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና የሃይማኖት አባቶች የምትሰሯቸው ስራዎችና በማንኛውም መንገድ የምታስተላልፏቸው መልእክቶች የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር እንጅ የሚሸረሽር እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ በማድረግ ወገናዊና አገራዊ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን።
4) በማንኛውም መለኪያ የቅማንትን ህዝብ የራስ አስተዳደር ጥያቄ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ግንባር ቀደም ተዋናይ የሚሆኑት ራሳቸው የጎንደር ህዝቦች በመሆናቸው ብሎም በጉርብትና ለዝንተ አለም አብረው የሚኖሩ እንደመሆናቸው መጠን በመካከላቸው ንፋስ የሚያስገቡ ቀዳዳዎችን ሁሉ በጋራ እንዲደፍኑ፣ በቅማንት ህዝብ በኩል የተነሳውን ህጋዊ ጥያቄም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን ሁሉ በመተሳሰብና በመግባባት እንዲፈቱ ከልብ እንመክራለን።
5) የጎንደር ወጣቶች ለመብታቸው የሚያደርጉትን ትግል የምናደንቅና የምናከብር ቢሆንም የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ በምክንያት ላይ የተመሰረቱና ከስሜት የጸዱ እንዲሆኑ፣ብሄር ሳይገድባቸው በመካከላቸው ያለውን ህብረት እንዲያጠናክሩ፣ ጎንደር ብዝሃንነቷንና አንድነቷን እንደጠበቀች ወደቀደመ ክብሯ እንድትመለስ የጋራ ቁርጠኛ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
6) የተረጋገጠ ማስረጃ በማይቀርብበት ሁኔታ የቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደር ጥያቄ የህወሃት እጅ አለበት እየተባለ በከንቱ ፍረጃ ህዝብን ለማወናበድና ለመጉዳት ተግተው እየሰሩ የሚገኙ አካሎች ሁሉ ከዚህ ፍጹም ሃላፊነት ከጎደለው ነውረኛ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አጥብቀን እንጠይቃለን።
7) በሌላ መልኩ ደራሽ የሌለው የቅማንት ህዝብ “በህወሃት ስም” ያለአግባብ ተፈርጆ ሲቀጠቀጥ የማይመለከታቸው መስለው አሻግረው የሚመለከቱ የህወሃት ባለስልጣናት ግልጽ ያለ የማስተባበያ መግለጫ በድርጅታቸው ስም ማውጣት አለመቻላቸው የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን የታሪክ ተጠያቂነትንም የሚያስከትል ጭምር በመሆኑ ይህንን እንዲያደርጉ በፖለቲካ ቁማርተኞች ግፍ በሚፈጸምበት የቅማንት ህዝብ ስም አጥብቀን እንጠይቃለን።
8) በጎንደር አካባቢ ከቅማንት ህዝብ ራስ አስተዳደር ጥያቄ ጋር በቀጥታ በተያያዘና በሌላም ጉዳይ ደረቅ ወንጀል ያልሰሩና በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እየተለቀሙ ወደ እስር የተወረወሩ ግለሰቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እንጠይቃለን።

ጎሰልፍ
ሰ/አሜሪካ
ነሃሴ 12 ቀን 2012 አ/ም

Leave a Reply