የቅማንትን ህዝብ የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄን አስመልክቶ ህዝብ ማወቅ ያለበት ዕውነታዎች፤
_________________________________________________

የቅማንትን ማንነት ለመበዬን የተነሱ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚገኙ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ሲያሰራጩ የቆዩትና በማሰራጨት ላይም የሚገኙት የተሳሳተ ትርክት ከዕውነታው በእጅጉ የራቀና የተለዬ፣ ይልቁንም በቅማንትና በአማራ ህዝቦች መሃከል ሆን ተብሎ ግጭት ለመፍጠርና ለማባባስ የታሰበ መሆኑን ከይዘቱ መረዳት ይቻላል። በሌላ መልኩ ሲታይ ደግሞ የቅማንት ህዝብ የሚፈልገውን የማያውቅ በአስተሳሰቡ ደካማ እንደሆነ አድርጎ የሚሳደብ፣ የብሄረሰቡን ማንነት በድፍረት እኔ ካልወሰንኩልህ የሚል ኢፍትሃዊና ኢዴሞክራሲያዊ ይዘት ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ ህዝብን የሚያሳስትና በመረጃ ያልተደገፈ አደገኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሆኖ በመገኘቱ የዚህን ጽሑፍ መውጣት አስፈላጊ አድርጎታል። የጽሑፉ ዋና አላማ የቅማንትን ህዝብ የማሳነስ፣ የመናቅና የማጠልሼት ተግባር ላይ ከመጠመዳቸውም በላይ ሌላው ህዝብ ስለቅማንት የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ላይ የተጠመዱትን ተነቅቶባችኋል ለማለት ነው። እንዲሁም ከነዚህ ውስጥ የብሄረሰቡ ተወላጆች ነን የሚሉ ጥቂት ግለሰቦች በሰሜን አሜሪካ የሚገኘውን የቅማንት ማህበረሰብ የሚወክሉ በሚመስል መልኩ በተለያዩ ሚዲያዎች እየቀረቡ ማህበረሰቡን በማይወክል፣ ይልቁን በሚሳደብና ከዕውነታው በራቀ መንገድ ላሰራጩት የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ዕርምት ለመስጠት ነው። ከተቀበሉትም- እነዚህን ግለሰቦች ከክፉ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡና ለዕውነት እንዲቆሙ ለመምከርና ለማሳሰብም ጭምር ነው። ይህን የሚያደርጉት የቅማንት ተወላጅ ግለሰቦች ቁጥራቸው ከአስር የማይበልጥ ሲሆን ለዚህ ድርጊት ያደፋፈራቸው ደግሞ የተሰጣቸው ተልዕኮ በመኖሩ እና ወጣንበት ስለሚሉት የቅማንት ማህበረሰብ ያላቸው ድሁር ግንዛቤ ነው። አቀራረባቸውም የቅማንትን ህዝብ ህይዎት እኛ አንምራልህ የሚል አይነት ነው። በሌላ አነጋገር የቅማንቱን ህዝብ ማንነትና ፍላጎት እራሳቸው ሊወስኑለት ይፈልጋሉ። የግል ሃሳብንና አመለካከትን መግለጽ ተገቢነት ያለው ቢሆንም ወክለኝ ያላለን ህዝብ በማን አለብኝነት ወክሎ በማንነቱ ላይ ለመበዬን በድፍረት መነሳት ግን ግዙፍ የአላዋቂነት ጫፍ አልያም ኢ-ፍታዊነት ይሆናል። በዚህ አድራጎታቸውም የቅማንት ህዝብ እንዲያዝንና ስሜቱ እንዲጎዳ አድርገዋል። እነዚህ ግለሰቦች የመንግሥት የጸጥታ ኃይልና ፋኖ በሉኝ ብሎ የተደራጀ የወንበዴ ቡድን ተባብረው ለቀጠፉት ብዙ ህይዎት ፣በእሳት ላወደሙበትና ለዘረፉት መጠነ-ሰፊ ሃብትና ንብረት በቀስቃሺነት የበኩላቸውን የወንጀል ድርሻ አበርክተዋል። በምላሳቸው የረጩት መርዝ በግፍ ለተቃጠሉ፣ ለታረዱ፣ ለተረሼኑና ለተፈናቀሉ አያሌ ቅማንቶች የእራሱ የሆነ አስተዋጽዖ እንዳደረገ የቅማንት ህዝብ በሃዘኔታ እየገለጸው ይገኛል።

እነዚህ በማወቅም ሆነ በግንዛቤ ድሁርነት የቅማንት ተወላጅነታቸውን መልሰው ቅማንትን ለመጉዳት እየተጠቀሙበት የሚገኙ ግለሰቦች ይህን የመሰለውን መርዛማ የሃሰት ትርክታቸውን የሚረጩት በተለያዬ ጊዜና በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች እየቀረቡ ነው። እነዚህ ሚዲያዎች ኢሳት፣ ዘ-ሐበሻ፣ አስራት ሚዲያና ሕብር ሬዲዮ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙት ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች በ1999 ዓ.ም በተደረገው የቤቶችና የህዝብ ቆጠራ ማንነቱ መሰረዙን የተረዳው የቅማንት ህዝብ በመረጣቸው ወኪሎቹ አማካኝነት ማንነቱን ለማስመለስ ሰላማዊና ሕጋዊ እንቅስቃሴ እንደጀመረ በኢሳት ቴሌቪዢን ወጥተው እንቅስቃሴውንና ወኪሎችን ማብጠልጠል የጀመሩ እና የአወገዙም ናቸው። ሆኖም እነዚህ ከቅማንት መወለድ ቅማንትን የመሳደብና የማፈን መብት የሚሰጥ የሚመስላቸው ጥቂት የቅማንት ተወላጆች የቱንም ያህል ቢደክሙ የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም። ለዚህም ዋናው ምክንያት የሚነሱት ከራሳቸው የግል ስሜትና ፍላጎት እንጅ ከቅማንቱ ህዝብ ፍላጎት ባለመሆኑ ነው። እንደማሳያም የቅማንት ህዝብ ጥያቄ የተነሳው በሶስተኛ ወገን ተገፋፍቶ ነው ይላሉ። የማንነቱ መሰረዝ ለቅማንት ህዝብ የማንነትና የእራስ አስተዳዳር ጥያቄ መነሳት በቂ ምክንያት ነው ብለው አይቀበሉም። የቅማንት ህዝብ ስለማንነቱ ያለውን ግንዛቤ የሚለኩት በእነሱው ቁንፅል ሓሳብ ልክ ነው። እናም “ቅማንት ከአማራ የተለየ ማንነት የለውም፣ ስለሆነም የማንነት ጥያቄ የለውም፣ ጥያቄው የወያኔ ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ነው፣ የቅማንት ኮሚቴ የቅማንትን ህዝብ አይወክልም፣ ኮሚቴው መቀሌ ጽ/ቤት አለው፣ ጎንደርን በቅማንት አማካኝነት ከትግራይ ጋር የመቀላቀል እቅድ አለ፣ ወዘተ” በማለት ያለምንም መረጃና ማስረጃ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይደሰኩራሉ። አገሪቱ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በፍጹም አልተረዱትም:: በእጅጉ ኢ-ዲሞክራሲያዊና ኢ-ፍትሐዊ ስለሆኑ የህዝቦችን ጥያቄ ከቅማንት ላይ ሲደረስ ደረቅ ባንክ ያደርጉታል:: በነዚህ ግለሰቦች የሚቀርበውን ከመረጃ የተፋታ ክስ የኢሳት ሚዲያ እየተቀበለ በተለያዬ ጊዜ ሲያስወነጭፈው ቆይቷል። እንዲሁም ከጎንደር መግደል፣ ማሳደድና ማሰርን የተፈጥሯቸው አካል እስኪመስል ይተጉ የነበሩት የአማራ ክልል ጨፍጫፊ የጸጥታ ባለስልጣናት በግልጽ በሚታይ ንቀትና ጥላቻ ተሞልተው የሚያቀርቡትን በመረጃ ያልተደገፈ ክስ የሞራልም ሆነ የሙያ አጥር ሳያግደው በማናለብኝነት እየተቀበሉ አሰራጩት። የቅማንት ህዝብ ግን እስካሁንም ለእነዚህ መሰረተ-ቢስ ክሶች ተጓዳኝ መረጃዎችን በመጠበቅ ላይ ይገኛል።

በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በቅማንት ህዝብ ላይ በመረጃ ያልተደገፈ ክስ እያቀረቡ ህዝብን ከሚያሳስቱ የቅማንት ተወላጆች ውስጥ በኢሳት ሚዲያ ቀርበው ከአደረሱት ጥፋት ሳይማሩ በድጋሜ ከወራት በፊት አስራት በሚባል ሚዲያና በቅርቡ ደግሞ ሕብር ሬዲዮ የቀረቡት ይገኙበታል። እንደበፊተኞቹ ሁሉ በእነዚህም ወንድሞች የሚቀርበው ክስ የቅማንት ህዝብ ጥያቄውን ያነሣው /የደገፈው ተታሎ ነው በማለት የህዝቡን የጋራ ብስለትና ግንዛቤ ዝቅ የሚያደርግ ስድብና ውርደት ይግኝበታል። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው እነዚህ ግለሰቦች ሲያሰኛቸው ህዝቡ ጥያቄውን አይደግፈውም ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ ጥያቄውን የደገፈው ተታሎ/ተሼውዶ ነው ይላሉ። በዚህ ተቃርኖ ውስጥ ዕውነት የለም። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ግን አናዛዥ አበነብስ፣ አመሳካሪ ዳኛና ፈራጅ ህሊና በሌሉበት ዕውነት እንዴት እንደምትመነምን ነው። በተጨማሪም “የቅማንት ጥያቄ የሶስተኛ ወገን ነው፣ የቅማንት ኮሚቴ የቅማንትን ህዝብ አይወክልም፣ ጥያቄው የተፈጠረው ገንዘብ በተከፈላቸው ሰዎች አማካይነት ነው፣ ወዘተ” በማለት ሆን ብለው አልያም ተሳስተው እነዚህን ሚዲያዎች የሚከታተለውን ህዝብ በማሳሳት ላይ ይገኛሉ። ይህንና ይህን የመሳሰለው በመረጃ ያልተደገፈ ፕሮፓጋንዳ እጅግ ብዙ ዋጋ ያስከፈለና በማስከፈል ላይም እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። እዚህ ላይ አንድን ሃሳብ፣ መመሪያ፣ ፕሮግራም፣ እንቅስቃሴና የመሳሰሉትን አቋም ጠያቂ ሁኔታዎችን መደገፍም ሆነ መቃወም መብት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ያለመረጃ ስም ማጥፋት ወይም ማጠልሼትና መሳደብ ግን ወንጀል ይሆናል። ደግሞም ነው። የዚህ ጽሑፍ አላማ እነዚህን ወንድሞች ለመሳደብ አይደለም። እንዲያ ከሆነማ የአጥፊዎች ቁጥር ወደ ሁለት አደገ ማለት ነው። የእዚህ ጽሑፍ አላማ እነዚህ ወንድሞች እንዲሰራጭ ባደረጉት በመረጃ ያልተደገፈ ትርክት ግራ የተጋባ ወይም የተሳሳተ ሰው ቢኖር የትርክቱን ሌላ ገጽታ በማሳዬት ቢያንስ ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲፈጠር በትንሹም ቢሆን አስተዋጻኦ ለማድረግ ነው።

ከዚህ በመቀጠል ቅማንት ማን ነው? የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ለምን ተነሳ? በማን ተነሳ?፣ መቼ ተነሳ?፣ የቅማንትን ኮሚቴ ማን ፈጠረው? በቅማንት ህዝብና በኮሚቴው ላይ ያለመረጃ የሚቅረቡ ክሶች ምን ምን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች እያነሳን ባጭሩ እንዳስሳለን። ይህንም ስናደርግ ዕውነትን ወግነን እንጅ ሌላ እንዳልሆነ ከወዲሁ ለማስገንዝብ እንወዳለን።

የቅማንት ህዝብ ከክርስትና እና ከኦሪት በፊት የነበረውን ህገ-ልቦና በመባል የሚታወቀውን የመጀመሪያውን በአንድ አምላክ አምልኮ ወይም ዕምነት ይዞ የዘለቀ ወይም የኖረ ጥንታዊ ህዝብ ነው። ህገ-ኦሪት ወይም ህገ-ሙሴ እና ክርስትና ህገ-ልቦናን ተከትለው የመጡ ብቻ ሳይሆን የነባሩን የህገ-ልቦና ዕምነት ትውፊቶችና ቁሶችም በውርስነት ይዘው የመጡና የቀጠሉ መሆናቸው ይታወቃል። ለምሳሌ የህገ-ልቦና ዕምነት ይከናወን የነበረው በድግና ውስጥ ነበር። የኦሪትን መምጣት ተከትሎ ድግናው ቤት ተሰርቶበትና የሙሴ ጽላት ገብቶበት ወደ ሙክራብነት ተለወጠ። በኋላም ክርስትና ሲመጣ ደግሞ መስቀል ታከለበትና ወደ ዛሬው ቤተ-ክርስቲያንነት ተቀየረ። ዛሬ እንደሚታየው በገጠርና በከተማ የሚገኙ ቤተ-ክርስቲያኖች በድግና ውስጥ ለመገኘታቸው ምክንያቱ ይህ ነው። ከለውጥ፣ ልምድና ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ከህገ-ልቦና ወደ ህገ-ኦሪት በተደረገው ሽግግር ሁሉም የህገ-ልቦና ተከታይ በአንድ ጊዜና በአንድነት አዲስ ወደ መጣው የኦሪት ዕምነት በቀላሉ ተለውጦ እንደማይሆን መገመት አይቸግርም። ከኦሪት ወደ ክርስትና በተደረገው ሽግግርም እንዲሁ። በመሆኑም የተወሰነው የህገ-ልቦና ተከታይ አሪትን ሲቀበል ሌላው ነባሩን ዕምነት እንደያዘ ቀረ። ዛሬ ቅማንት በመባል የሚታወቀው ህዝብ ይህን የህገ-ልቦና ዕምነት ይዞ የቀረው ህዝብ ነው። ኦሪትን የተቀበሉት ደግሞ ቤተ-እስራኤል ሲባሉ የኖሩትና በኋላ ላይ ፈላሻ በሚል አማራጭ ወይም ተደራቢ ስም የሚታወቁት ናቸው። በኋላም ክርስቲያን (አማራ) የሆኑት ህገ-ልቦናዎችና ቤተ-እስራኤሎች ወይም ፈላሾች ናቸው። ለዚህም ነው በአንድ ቅማንት፣ አማራና ቤተ-እስራኤል መሃከል ምንም ዓይነት የመልክ ልዩነት የሌለው። እነዚህ ሶስቱ በህገልቦና ጊዜ አንድ ህዝብ የነበሩና ኋላ ላይ በዕምነት ምክንያት ከሶስት የተከፈሉ ናቸው። የአጥንት፣ የደምና የቆዳ ልዩነት የላቸውም። በእምነት ሳቢያ ተለያይተው በኖሩበት እረጅም ጊዜ ግን የእየራሳቸውን ስነልቦና መፍጠራቸውና ማዳበራቸው አልቀረም። ቅማንት ማነው ስለሚለው በአጭሩ ይህን ያክል ካልን በኋላ ወደ ማንነትና የእራስ አስተዳደር ጥያቄው አነሳስ እንሻገራለን።

በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በተለይ ደግሞ በጎንደር ውስጥ በርካታ የወንዝ፣ የተራራና የቦታ ስሞች የቅማንትኛ ድምጽ/ልሳን አላቸው። እነዚህ ከድግና ጋር ተደምረው ሲታዩ ቅማንት ነባርና ጥንታዊ ህዝብ መሆኑን ያመለክታሉ። እጅግ የሚበዛው የህገልቦና ወይም የቅማንት ህዝብ በጊዜ ብዛት ክርስትናን እየተቀበለ ወደ አማራነት ቢቀየርም እስካሁንም ግን አማራ ነን ሳይሉ ወይም አማራ ናችሁ ሳይባሉና ቅማንት ነን እያሉ በቅማንትነት ስነልቦና ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች አሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ቤቶችና ህዝብ ቆጠራ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶም የራሳቸው የሆነ መቆጠሪያ ኮድ ተሰጥቷቸው ይኖሩ ነበር። በ1999 ዓ.ም በተደረገ የቤቶችና ህዝብ ቆጠራ ግን ሳይጠየቁና ሳያውቁት የመቆጠሪያ ኮዳቸው ተሰርዞ ሌሎች በሚል ተተካ። ህዝቡም በሁኔታው አዝኖና ተቆጥቶ ማንነቱን ለማስመለስ ቆርጦ ተነሳ። ለተግባራዊነቱም ትግሉን የሚያስተባብርለት የቅማንት የማንነትና የእራስ አስተዳደር ኮሚቴ መረጠ። ትግሉ ህጋዊና ሰላማዊ እንዲሆን ተወስኖ እንቅስቃሴ ተጀመረ። እንግዲህ መንግሥት ማንነታቸውን በመሰረዙ ምክንያት የተፈጠረውን ይህን አብይ የህዝብ ጥያቄና መሪ ኮሚቴውን ነው ከላይ የተጠቀሱት ወንድሞችና ሌሎችም ቅማንት ጠል ኃይሎች እየተነሱ የሶስተኛ ወገን ነው እያሉ ስሙን የሚያጠለሹት። ይህ ግን የንቀት እና የኢ-ፍታዊነት ማሳያ ከመሆን ያለፈ ትርጉም የለውም። እዚህ ላይ ግልጽ ያልሆነው ጉዳይ የህዝቦችን/ብሔረሰቦችን ማንነት ከምታከበር አገር ውስጥ የማንነት ጥያቄ ከቅማንት ላይ ሲደርስ ለምን የሶስተኛ ወገን እንደሚባል ነው። እነዚህ ጥያቄው የሶስተኛ ወገን ነው የሚሉ ኃይሎች ጥያቄውን ከማጠልሼት አልፈው የቅማንቱን ማንነት እራሳቸው ሊበይኑለት ሲኳትኑም ይታያሉ። ይህ በሃሰትና በሴራ የተሞላ የጨለማ መንገድ ምን ያህል ዕርቀት እንደሚወስዳቸው የሚታይ ይሆናል። የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ግን ከላይ እንደተጠቀሰው ህዝብ እንዳይሳሳት ሲባል በቅማንት ህዝብና በኮሚቴው ላይ የሚወርደው የክስ ናዳ ቢያንስ በመረጃ ያልተደገፈ መሆኑን ለማሳዬት ጭምር ነው። እዚህ ላይ በድጋሚ ግልጽ መሆን ያለበት ክሱን በማስረጃ አስደግፎና ጥያቄውንም ባመክንዮ መሞገት መብት ብቻ ሳይሆን ተገቢም መሆኑን ነው። እራስንና የጥያቄውን ባለቤት ወክሎ ያለመረጃ ከሳሺና ፈራጅ በመሆን በሌላ ማንነት ላይ ለመበየን መነሳት ግን ተራ ጠላትነት ካልሆነ ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም።

እነዚህ ምክንያት አልባ ቅማንት ጠሎች ከሚያቀርቧቸው በመረጃ ያልተደገፉ ክሶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል። “ጥያቄውን ህዝቡ አይደግፈውም፣ ደጋፊ ካለም ተገዶ ነው፣ ጥያቄው የተነሳው በሶስተኛ ወገን ግፊት ነው፣ ጥያቄውን ያስነሱት በገንዝብ የተገዙ ጥቂት ካድሬዎች ናቸው፣ ኮሚቴው በህዝብ አልተመረጠም፣ ኮሚቴው የሶስተኛ ወገን ተላላኪ ነው፣ ወያኔ በማረካቸው የቅማንት ተወላጅ በሆኑ የደርግ ወታደሮች የሚያንቀሳቀስ ጥያቄ ነው፣ ወዘተ” የሚሉት ይገኙበታል። እነዚህን የአሉባልታ ክሶች ቀደም ሲል የነበሩ የክልሉ ባለስልጣናትም የቅማንትን አንገት ለማስደፋት በስፋት ይጠቀሙባቸው እንደነበር ይታወሳል። በተለይም የጸጥታ ክፍሉ ሲያቀርባቸው የነበሩ አስፈሪ ክሶች በቅማንት ህዝብ ላይ የታሰበውን አደጋ ከመጠቆም ያለፈ ታማኒነት አልነበራቸውም። ከእነዚህ ውስጥ በሶስት ቀበሌዎች ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተገኘ፣ ከሌላ ቦታ የመጡ ተዋጊዎች በውጊያ ላይ ተማረኩ፣ በአካባቢው ሊገኝ የማይችል የጦር መሳሪ ተማረከ የሚሉት ይገኙበት ነበር። በውጭ ያሉትንና እነዚህን የክልል ባለስልጣናት ጨምሮ መረጃ አለን ከማለት አልፈው ለአንዱም ክስ አንድም ቀን መረጃ አቅርበው አያውቁም። እነዚህ ውጭና ውስጥ የሚገኙ ቅማንት ጠል ቡድኖች እየተናበቡ እንደሚሰሩ ከድርጊታቸው መረዳት ይቻላል። የእነዚህ ኃይሎች የተቀነባበረ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ወደ ተግባር ተመንዝሮ በቅማንት ህዝብ ላይ ያደረሰውን ከባድ ጥፋት አሁን ላይ የዓለም ህዝብም ሳይቀር እየተረዳው እንደሆን መረጃዎች ያሳያሉ። በገዛ ወገን ላይ እንዲህ አይነቱ የስም ማጠልሼትና የጥፋት ዘመቻ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል እንላለን። በውጭና በውስጥ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከላይ ለተጠቀሱት ክሶች ማስረጃዎች ዬት አሉ ብሎ እንዲጠይቅና ከዕውነት ጎን እንዲቆም እያሳሰብን ይህ ጽሁፍም ጠቃሚ እንደሚሆንም ተስፋ እናደርጋለን።

ከሰላም፣ ልማትና ፍትህ ለጎንደር (ጎሰልፍ) ማህበር
ሰሜን አሜሪካ
ሰኔ 24/2012

Leave a Reply